Improved Coffee Seedlings Being Prepared
Back

Improved Coffee Seedlings Being Prepared

ECTA
5 min read

የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች እየተዘጋጁ ነው

ታኅሣስ /2018

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ የቡና ዝርያ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

230 ሺህ አርሶ አደሮች ከ120 ሺህ ሔክታር በሚልቅ መሬት ቡና እያለሙ እንደሚገኙ በጽሕፈት ቤቱ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ቡድን መሪ ኦሉማ በዳኔ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የቡና ልማትን ለማስፋት በ12 ቡና አብቃይ ወረዳዎች በመጪው ክረምት የሚተከሉ ከ41 ሚሊየን በላይ ምርታማነታቸው የተሻሻለ የቡና ዝርያ ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከ20 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በቡና ችግኝ ዝግጅት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመው፤ ችግኞቹም በአብዛኛው ከዚህ ቀደም ባልተሸፈነ ሰባት ሺህ ሔክታር ላይ በመጨው ክረምት እንደሚተከሉ አመላክተዋል።

በዞኑ የቦኬ ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ መሀመድዘይን አብደላ በበኩላቸው፤ የቡና ልማትን ለማስፋፋት ለአርሶአደሮች የተሻሻለ የቡና ዝርያ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለዚህም በችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች ከ3 ሚሊየን በላይ የተሻሻለ የቡና ዝርያ ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

የቡና ችግኞቹ በሁለት ዓመት ውስጥ ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸው፤ በችግኝ እንክብካቤው ከ2 ሺህ በላይ አርሶአደሮች መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡

በቦኬ ከተማ ዙርያ በቡና ችግኝ እንክብካቤ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው አይሻ አሕመድ ባለፉት ዓመታት የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን በማሳቸው በመትከል ገቢያቸውን ማሳደጋቸውን ለኢዜአ ገልፀዋል።

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3
Gallery image 4
Gallery image 5

Tags

#ECTA#coffee