እሴት የተጨመረበት የቡና ምርት ገበያ
Back

እሴት የተጨመረበት የቡና ምርት ገበያ

ECTA
5 min read

ኢትዮጵያ እሴት የተጨመረበት ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ገቢዋን ለማሳደግ እየሠራች ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2018: ኢትዮጵያ ቡናን በጥሬው ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ ለዓለም ገበያ በማቅረብ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ።

ኢትዮጵያ የቡና መገኛና ከአፍሪካ ቀዳሚዋ አምራች ሀገር ስትሆን ቡናን እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ በመላክ የተጀመረው ጥረት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ 470 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የ15 ዓመት የቡና ስትራቴጂ ፍኖተ ካርታ ተቀርጾ ወደ ሥራ ተገብቷል።

በዚህም በዘርፉ የነበሩ መዋቅራዊ ችግሮችን በመለየት በምርትና ምርታማነት እንዲሁም በገበያ አድማስ ማስፋት ላይ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

ምርታማነታቸው ዝቅተኛ የነበሩ ያረጁ የቡና ተክሎችን በመጎንደል የማሳ ላይ ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

በሀገር አቀፉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ታግዞ አዳዲስ የቡና ተክሎች በስፋት መተከላቸውን ጠቁመዋል።

በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የምርት መጠን ብቻ ሳይሆን ጥራት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ቡናው በከፍተኛ ጥራት እንዲመረት ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ምርታማነትን ከማሳደግ ጎን ለጎን የግብይት ሰንሰለቱን ማሳጠር ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ለውጥ እየመጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል የነበረውን የተንዛዛ የገበያ ሥርዓት በፖሊሲ ማሳጠር በመቻሉ ይባክን የነበረውን የምርት መጠን መቀነስና በጥራት ላይ ይፈጠሩ የነበሩ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ማስቀረት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካላት የቡና አቅም አንጻር የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ እሴት ጨምሮ ለገበያ የማቅረብ ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ቀደም ሲል እሴት የተጨመረበት ቡና በምን ዓይነት የጥራት ደረጃና ሁኔታ ወደ ውጭ መላክ እንዳለበት የሚወስኑ ግልጽ መመሪያዎች ባለመኖራቸው ዘርፉ ሳይነቃቃ መቆየቱን አስረድተዋል።

ይህንን ክፍተት በመሙላት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር አዲስ መመሪያ ጸድቆ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመው አዲሱ መመሪያ በሀገር ውስጥ የተቆላና የተፈጨ ቡናን በውጭ ምንዛሬ የመሸጥ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በርካታ የቡና ቆይ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በትላልቅ ሆቴሎችና በቱሪስት መዳረሻዎች በውጭ ምንዛሬ መሸጥ መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡

Gallery

Gallery image 1

Tags

#ECTA#coffee