መስከረም 25/2018 ዓ.ም
ማና
ላለፉት ቀናቶች በስፔሻሊቲ ቡና ላይ በንድፈ ሀሳብ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ማጠናከሪያ በዛሬው እለት በተግባርም ሲሰጥ ውሏል።
የተግባር ስልጠናው ከመጀመሩ በፊት የጅማ ዞን ግብርና ጽ/ቤት የቡና አግሮኖሚ ባለሞያ አቶ ሞቱማ ገርባባ ስለስልጠና ቦታው ገለጻ አድርገዋል። በገለጻቸው የስልጠና ቦታው የማና ወረዳ የቡና ዘር ዝግጅት ማሳያና ማዘጋጃ እርሻ ቦታ እንደሆነ ገልጸዋል። በማሳያው እርሻው የሚገኘው ቡና ቫራይቲው 74110 እንደሆነና የማሳያው የዘር ምርት ውጤት ለአርሷደሩ ጠቀሜታ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል። የማሳያው ዋነኛ ዓላማ ግን አርሷደሩ የቡና ዘር ዝግጅት ትምህርት የሚያገኝበትና ክህሎት የሚቀስምበት እንደሆነ አስረድተዋል። መሰል ማሳያዎች በሌሎች የጅማ ዞን ወረዳዎች ማለትም በሊሙ፣ ጉማይ፣ ዴዶ፣ ጎማ እና ጌራ ወረዳዎች እንዳሉ አሳውቀዋል። ማሳያዎቹ በሙሉ በመንግስት የለሙ እንደሆነ ገልጸው የየወረዳዎቹ አርሷደሮች ዘር እንዴት እንደሚዘጋጅና እንደሚከማች ይማሩበታል ብለዋል።
አቶ ሞላ ደምሴ የኢቡሻባ የድኅረ ምርት ዝግጅት ከፍተኛ ባለሞያ እንዳሉትም እንደተጠቀሱት ያሉ ማሳያዎች በሌሎች ቡና አብቃይ ክልሎች መኖር እንደሚገባ አስገንዘበው በከፋ ዞን አንዳንድ አርሷደሮች በዘር ዝግጅት ተግባር እንደተሰማሩ አስታውሰው ሆኖም ግን በመንግስት የተዘጋጁ ማሳያዎች ካሉ መልካም እንደሆነና ከሌሉም ሊኖሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። በማስከተልም ከስፔሻልቲ ቡና አዘገጃጀት ጋር በተያያዘ በንድፈ ሀሳብ ያሰለጠኑትን የዘር አዘገጃጀት ክፍልን የከለሱ ሲሆን ለዘር የሚሆነው ቡና ምን አይነት ቡና እንደሆነ አስረድተው ለዚህ ዓላማ ያልዋሉ ቡና ለገቢ ምንጭ ማስገኛነት እንደሚውሉ ገልጸዋል። የቡና ዘር ዝግጅት ስራ ተሰራ ማለት በተጓዳኝ የቡና ዛፍ እንክብካቤ እና የአፈርና ውሃ ልማት ስራ ግድ አብሮ የሚሰራ ስራ እንደመሆኑ በዚህ ረገድም ዕውቀትና ክህሎት የሚገኝባቸው ማሳያዎች እንደሆኑ አስረድተዋል።
በማስከተልም ሠልጣኞቹ በንድፈ ሀሳብ በሠለጠኑት መሠረት ከቡና ዛፍ ላይ የቡና ለቀማ፣ በሶርቲንግ ባእድ የሆኑ ነገሮችንና ተገቢ ያልሆኑ ቡናዎችን የመለየት እና በተንሳፋፊ የተሻሉ ቡናዎችን የመለየት ክህሎቶችን በተግባር ሰልጥነዋል።
በስተመጨረሻም ስልጠናውን ያዘጋጁት የኢቡሻባ የስትራቴጂና ልማት ስራ አስፈጻሚ አቶ ቦንሳ መርጊያ ማጠቃለያ የሰጡ ሲሆን ስልጠናዎቹን የወሰዱት አካላት ወሳኝ አካላት እንደሆኑ ታምኖበት ስልጠናውን እንዲወስዱ መደረጉን አስረድተው ከዚህ ቀደም የልማት ሰራተኞች ብቻ ስልጠናውን ሲወስዱ እንደነበር፤ በዚህ ስልጠና ግን አርሷደሩ ራሱ እንዲሰለጥን መደረጉን ገልጸዋል። ይህ መሆኑ ደግሞ ከስልጠናው መልስ በማሳዎቻቸው ሲተገብሩ መደናገር በሌለበት መልኩ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚጠቅማቸው መሆኑን እናምናለን ብለዋል። በዚህም መሠረት ከኮኦፐረቲቭ 60፣ ከባለሞያዎች 20 ሰዎች ስልጠናውን እንዲወስዱ ተደርጓል ያሉ ሲሆን ስብጥሩ ወሳኝ እንደሆነና በዚህ መልኩ ስልጠናው ሲሰጥ ተጨባጭና ፈጣን ለውጥ ይመጣል ተብሎ ይታመናል ብለዋል።
ስራ አስፈጻሚው በስተመጨሰሻም የሰለጠኑትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ ግብዓቶችን የሟሟላት ስራ ሲሰራ እንደቆየ አስታውሰው በቀጣይም ግብዓት የማሟላት ተግባሩን ለመቀጠል የግዥ ሂደቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው ሠልጣኞቹ የሰለጠኑትን ተግብረው ለውጥ እንዲያመጡና ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በአካባቢያቸው ለሚገኙ አርሷደሮች እንዲያካፍሉ አሳስበዋል።






