በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ስር የሚገኘው የቡና ማሰልጠኛ ማእከል በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በዛሬው እለት አስመረቀ!!!
06/04/ 2018
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ስር የሚገኘው የቡና ማሰልጠኛ ማእከል በተለያዩ የቡና ሙያ መስክ ያሰለጠናቸውን 76 ተማሪዎች ክቡር ዶ/ር አዱኛ ደበላ፣ ክቡር አቶ ሻፊ ዑመር፣ ክቡር አቶ ታጋይ ኑሩ፣ የተባበሩት መንግስታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት/UNIDO ተወካይ ዶ/ር ካሳዬ ቶሌሳ፣ የባለስልጣን መ/ቤቱ የተለያዩ የስራ ክፍል ሃላፊዎች፣ መምህራን እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት አስመርቋል::
የማዕከሉ አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ፍሬህይወት አሰፋ እንዳሉት ማዕከሉ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ከ500 በላይ ሙያተኞች ሰልጥነው መመረቃቸውን እና በርካታዎቹም በተለያዩ የዘርፉ ኢንዱስትሪዎች በስራ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፤ የዛሬዎቹ ተመራቂዎች ደግሞ በቡና ቅምሻ ለ11ኛ ጊዜ 39 ባለሙያዎች፤ በባሬስታ ለ14ኛ ዙር 13 ባለሙያዎች፤ በቡና ግብይትና ኤክስፖርት ዶክመንቴሽን 24 በድምሩ 76 ባለሙያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል ፡፡
ክቡር ዶክተር አዱኛ ደበላ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በምረቃው ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎች የምስክር ወረቀት በሰጡበት ወቅት ባሰሙት ንግግርም፤ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የኢትዮጵያን የቡና ጥራት ለማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ እና ከዚህም ውስጥ የቡና ማሰልጠኛ ማእከል በመክፈት በቡናው ዘርፍ ሰልጣኞችን በመቀበል በተለያዩ የቡና ሙያዎች በማሰልጠን ስራ ፈጣሪ ዜጎችን በመፍጠር የራሳቸውን ስራ እና በገበያው ተቀጥረው እንዲሰሩ እድል ማመቻቸቱን ጠቁመዋል። የቡና ጥራት መቆጣጠሪያ እና ሰርተፊኬሽን ማእከላትንም በተለያዩ የቡና አብቃይ ክልሎች በመክፈት የቡናችንን ጥራት በትኩረት እየተከታተለ ነው ካሉ በኋላ እናንተ የቡና ሙያ ተመራቂዎችም በተሰማራችሁበት የስራ ዘርፍ ሁሉ የኢትዮጵያን ቡና በማስተዋወቅ የቡና አምባሳደሮቻችን ሆናችሁ እንደምታገለግሉ እንተማመናለን ብለዋቸዋል፡፡
ዶ/ር ካሳዬ በበኩላቸው የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ከባለስልጣን መ/ቤቱ ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ቡና ዘርፍ በተለይም ለጥራት መሻሻልና ምርታማነት መጨመር የተለያዩ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ የሰለጠነ የሰው ሀይል በማፍራት ዘርፉ የሚፈልገውን የላቀ አቅም ለመፍጠር አሁን ካለው የቡና ማሰልጠኛ ማእከል በተጨማሪ ሰልጣኞችን ተደራሽ ለማድረግ ወደ ሌሎች ክልሎችም ለማስፋት እቅድ እንዳለው ጠቁመዋል።
የዛሬ ተመራቂዎች ከዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላና ከኢቡሻ የቡና ልማት ዘርፍ ሃላፊና ምክትል ዋናዳይሬክተር ከአቶ ታጋይ ኑሩ እጅ ሰርተፊኬት የተቀበሉ ሲሆን የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ሃብታሙ መብራቱ ዘግቦታል።











