በዞኑ በሻይ ልማት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል
ታህሳስ 26/2018
በኢሉ አባቦር ዞን ሻይን በኩታ ገጠም በማልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸው ተመላከተ።
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኢንሼቲቭ ተቀርጾላቸው በአዲስ መልክ እየለሙ ካሉ የእርሻ አይነቶች ውስጥ ሙዝ፣ አቮካዶ፣ ሩዝና ሻይ ተጠቃሽ ናቸው።
የሻይ ልማት ኢንሼቲቭ በኢሉባቦር ዞን በአብዛኞቹ ወረዳዎች እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን ባለፉት ሶስት ዓመታት በተለይም በመቱ፣ አሌና ሐሉ ወረዳዎች በስፋት በኩታ ገጠም እየለማ ይገኛል።
በተያዘው የበጋ ወቅትም ባለፈው ክረምት የተተከሉና በችግኝ ጣቢያዎች ላይ ያሉ የሻይ ችግኞችን የመንከባከብ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በ2018/2019 የሚተከሉ ችግኞችን የማዘጋጀት ስራ ትኩረት መሰጠቱን የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ አወል መሐመድ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በዚህም ሁሉን የልማት አቅም በማሳተፍ 250 ሚሊዮን የሻይ ቅጠል ችግኞችን ለማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
የችግኝ ዝግጅት ስራው ሰፊ የሰው ኃይል የሚፈልግ በመሆኑ በወረዳዎች በወል አቅም በሕብረተሰብ ንቅናቄ ታግዞ የሚሰራ መሆኑም ተገልጿል።
በመቱ ወረዳ በሻይ ልማት ተደራጅተው የተሰማሩ አርሶአደሮች፤ በአሁኑ ወቅት የተተከለ የሻይ ተክል በመንከባከብ ስራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሻይ ልማት ስራውን የማስፋት እቅድ ያላቸው መሆኑን ተከትሎ ደግሞ በችግኝ ዝግጅት ስራውም እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሻይ ልማት ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውልና ከችግኝ ዝግጅቱ ጀምሮ ሰፊ የሰው ኃይል የሚፈልግ በመሆኑ በዞኑ ትልቅ የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መስክ መሆኑም ተገልጿል ።

