ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም
ሐዋሳ
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከአርሷደር ማሳ እስከ ኤክስፖርት ድረስ የቡና ዱካ ክትትልን ዲጂታላይዝ ከማድረግ አንጻር ቩልካን በተባለ ድርጅት በኩል ያበለጸገውን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ከማድረግ በፊት የሙከራ ትግበራ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር የቅድመ ትግበራ ውይይት አካሂዷል። በዚህ የውይይትና ምክክር መድረክ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ የደን ልማት፣ የጂ አይ ዜድ ፣ የባለስልጣኑ ኢዩ ካፌ ፕሮጀክት ተወካዮች ከአዲስ አበባ፤ ከሲዳማ ክልል ደግሞ የክልሉ ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች እና የEUDR ፎካል ተወካዮች እንዲሁም የክልሉ የግብርና ባለሞያ ተገኝተዋል።
የውይይት መድረኩን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የአይ ሲቲ ስራ አስፈጻሚና የትሬሴቢሊቲ ፕሮጀክት አስተባባሪ ወ/ሮ ሐዊ አቶምሳ በንግግር የከፈቱ ሲሆን ቴክኖሎጂውን የማበልጸግ ሂደት ምን ይመስል እንደነበር በአጭሩ ገለጻ ያረጉ ሲሆን በበለጸገው ቴክኖሎጂ ላይ ተደጋጋሚ የውይይትና መድረኮች ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ከተውጣጡ ተወካዮች የተቋቋመው ታስክ ፎርስ ጋር ውይይት ተካሂዶ በተገኙ ግብዓቶች ቴክኖሎጂው ዳብሮ የመጨረሻ ደረጃ ላይ መድረሱ ታምኖበት የሙከራ ትግበራ ለማድረግ በክልሉ የሚመለከታቸውን አካላት በመያዝ እንደተገኙ ገልጸዋል። በኤክስፖርት ረገድ ጥራት ያለውን ቡና አቅርቦ ክልሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ መምጣቱን ያደነቁ ሲሆን በዚህም የሙከራ ተግባሩን ለማከናወን ክልሉን ተመራጭ እንዳደረገው ጠቅሰዋል። ለዚህም የሚመለከታቸው የክልሉ አካላት ላደረጉት ትብብር ምስጋናን አቅርበዋል። ከዚህ መድረክ በኋላም ባሉት ቀናቶች በሸበዲኖ ወረዳ በመገኘት ሲስተሙን በተግባር የማየት ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ከስራ አስፈጻሚዋና ፕሮጀክት አስተባባሪዋ በመቀጠል ሲስተሙን ያበለጸገው ቩልካን የተሰኘ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ኃላፊና ባለሞያ ቴክኖሎጂውን ያቀረቡ ሲሆን በምን መልኩ በቴክኖሎጂው ከቡና ማሳ ጀምሮ እስከ ኤክስፖርት ክትትል እንደሚደረግ አብራርተዋል። በዚህ ሲስተም ማንኛው የባለስልጣኑ የቡና መረጃ ማስተዳደር እንደሚቻል የገለጹ ሲሆን ለዚህም የተዘገጀ የሞባይል አፕልኬሽን እንዳለ አስረድተዋል። አፕልኬሽኑ የቡና አርሷደር፣ የቡና እርሻ እና የቡና ምርት መረጃ ለመያዝና መረጃዎቹን ወደሚመለከተው አካል ለመላክ እሚያስችል እንደሆነ ያስረዱ ሲሆን ከኢዩዲአር ጋር በተያያዘ ሲስተሙ ከደን ነጻ የሆነ የቡና ምርት ሂደት መረጃን ለመያዝ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በዚሁ ሲስተም ላይ የተደረጉ ውይይቶች በዜና እወጃ ያስታወቅን መሆኑ ይታወሳል፡፡
አሸናፊ ጌታሁን ዘግቦታል፡፡







