በ1ኛዉ ሩብ ዓመት ወደ 4ሺህ 1መቶ ቶን የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መቻሉን የክልሉ ቡና ፣ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በቡና ልማት ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎች ከክልሉ ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበውን የቡና ምርት መጠን እና ጥራት ለማሳደግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንዳለም ተጠቅሷል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክትር አቶ አስራት መኩሪያ እንዳሉት፣በክልሉ አምና ካደረዉ ምርት በአንደኛዉ ሩብ ዓመት ለማዕከላዊ ገበያ ለመላክ ከታቀደዉ 6ሺህ 220ቶን እስከ መስከረም 30 ድረስ ከ4ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል፡፡
ካደረዉ ቡና እስካሁን በክምችት የሚገኝ ቡና ኦዲት የማድረግና የመለየት ስራዎች መሰራታቸዉንና ይህም ከአዲስ ቡና ጋር ሳይቀላቀል ተሽጦ እንዲያልቅ ይደረጋልም ብለዋል፡፡
ክልሉ በ2017 በጀት ዓመት 48 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ያቀረበ ሲሆን በክልሉ አጠቃላይ ከምመረተዉ የቡና ምርት አንጻር ለገበያ እየቀረበ ያለዉ ምርት መጠን አነስተኛ መሆኑ ገልፀዋል፡፡
ባለስልጣኑ በዘንድሮ ዓመት በቡና ምርት ጥራት፣አቅርቦት እና በግብይት ስርዓቱ ላይ ለየት ባለ መንገድ በትኩረት በመስራት ቡናን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ሰፊ እንቅስቃሴ የተጀመረ መሆኑን ጠቁመዉ ከዚህም አንጻር ዓምና የነበረዉን አፈጻጸም በመገምገም በበጀት ዓመቱ የተሻለ ዉጤት ለማስመዝገብ ግብ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዘንድሮ በጀት ዓመት ወደ 71ሺህ 4መቶ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰዉ በመሰረታዊነት ከለየናቸዉ ነገሮች መካከል የአቅርቦት መጠን ከፍ ማድረግ፣የቡና ግብይት ስርዓቱ ህጋዊ እንዲሆን የሚስተዋሉ ህገወጥ የቡና ዝዉዉር መከላከል እና ጥራቱን ማስጠበቅ ነዉ በማለት ተናግረዋል፡፡
በሰዉ ሰራሽ ምክንያቶች የሚከሰቱ የጥራት መጓደል ችግሮችን በመቅረፍ በዘንድሮ ዓመት ከደረጃ ሶስት በታች መዉጣት የለበትም የሚል ጽኑ አቋም በመያዝ ወደ ስራ መገባቱም ጠቁመዋል፡፡
የታጠበ ቡና ምርት አዘገጃጀት እና ጥራት አጠባበቅ ላይ በክልሉ በከፍተኛ መጠን ቡና የሚያመርቱ ካፋ፣ሸካ እና ከቤንች ሸኮ ዞኖች ለተዉጣጡ የግብርና ባለሙያዎች፣የኢንዱስትሪ ባለቤቶች እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ስለጠና መሰጠቱንም አስረድተዋል።
ደረጃውን ያልጠበቀ መፈልፈያ ኢንዱስትሪ ፣ጥንቃቄ የጎደለው የቡና አደራረቅና አዘገጃጀት እንዲሁም በግብይት ማዕከላትና በተለያዩ ቦታዎች ጥንቃቄ የጎደለው አያያዝ ለቡና ጥራት ጉድለት ምክንያቶች በመሆናቸዉ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በእሼት ቡና አዘገጃጀት ላይ ያላቸውን ክፍተት ለመሙላት እና አቅም ለማሳደግ የሚረዳ ግንዛቤ ተፈጥሯል።
መረጃውን የወሰድነው ከደቡብ ምዕራብ ኮሚዩኒኬሽን ነው።




